የማይቀርበት መንገድ

0
267

አርባ ቀናት ሆኑ እንደዋዛ… አርባ እረፍት የሌላቸው ቀናት በሃሳብ የሚያባዝኑ:: የቁጭት ምነው እንዲህና እንዲያ ቢሆን የምልበት ብዙ መወትወት ማልቀስ ማዘን መቆዘም ደሞ ለመርሳት መሞከር…. ግን ከሰውም አለ የማይረሳ ሰው:: ስፈልግ እንደጓደኛ የምታማክር ሲያሻ እናት የምትሆን ሲላት እንደካህን ሌቱን ቆማ ብርቅባት እንኳ ስልክ አቃጭላ የምትፀልይ ስታገኘኝ ስስት የምሆንባት ፈገግ እያለች ብቻ ዝም ብላ የምታየኝ …. ልዮ ስሜት የምትሰጥ! እንደ እንቁ ተንከባክባ የከበረ ስሜት እንዲኖረኝ ስለራሴ የምታደርግ አስተዋይ ….እርሷ እስካለች ድረስ ፀሃይ ብትጠልቅ ፈገግታዋ ብቻ ጉሙን ይገፍልኛል የምላት ከእናት በላይ የሆነች እናት …. ምጡቅ አእምሮዋ ስታስተምር ካፏ መሬት ጠብ ሳይሉ ነበር ምክሮቿም ሆኑ ምሁራዊ አመክንዮዋ! ስትገስፅ አቅንታ ልታሳድግ ሲላት ደሞ ጓደኛ ሆና ሚስጥር የምትካፈል ሁለ ነገሬ ነበረች እናቴ ግን ደሞ የማይቀርበት መንገድ አለ:: ማስቀረት አልተቻለም! አንጀቷ እንዴት እንደቻለ እንጃ የልጆቿ ነገር የማይሆንላት ሰው ነበረችና:: ሁሉ ሰው በደግነቷ ያውቃታል:: ደግነት መጠሪያ ስሟ ነበር:: ምን ያደርጋል ቀን ሲደርስ ደግነትም አብሮ ሄዷል:: ቢከፋኝም ቢደላኝ እንግዲህ ብቻዬን ነኝ:: እናቴ የኔ ስስት ሁሌም በልቤ መቼም ላትወጪ ትኖሪያለሽ:: ወደ ምትወጂው ጌታሽ ወደ ተስፋው ክብር በክብር እንደተቀበልሽ አውቃለሁ:. አገልግለሽዋል በቃሉ ታምነሽ ኖረሻል:: ሩጫሽን ጨርሰሻል:: የድልን አክሊል ከእርሱ ከታማኙ ትቀበይ ዘንድ አለሽ! መሪር ብትሆንም ሃዘኔ ግን የሞት መውጊያ የተሰበረልሽ መሆኑን ሳስብ እፅናናለሁ:: በጌታ አንቀላፍተሻል እንጂ ሞት እንዳይዝሽ ያው መንፈስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው በአንቺ ውስጥ አለና ጌታን በምፅ አቱ ቀድመሽ እንደምትገናኚው አውቃለሁ:: በአብርሃም “አብርሃም አመነ ፅድቅም ሆኖ ተቆጠረት” በተባለ የምነት አባት ፈለግ ተከታይ ነሽና በአብርሃም እቅፍ እስከ ጌታ ቀን ትጠበቂ ዘንድ እንዳለሽ አውቃለሁና ልቤን በዚያ አፅናናለሁ:: ብዙ ሃሳብ ነበረን ብዙ እቅድ ብዙ ምኞትም ግን ጌታ የወደደው ሆኗል:: እግዚአብሄር ሰጠ እግዚአብሄር ነሳ ክብር ሁሉ ለሰምስይ ምድር ፈጣሪ ለነፍስ ሁሉ ጌታ ይሁን!! በከፍታም ሆነ በዝቅታ በሃዘንም ሆነ በደስታ ምስጋ. አይጓደልበት! እዚህ ለቅሶ ተብሎ ስናለቅስ በዚያ ደግሞ ሰርግ ነበር ወደ አባትሽ እቅፍ ስትገቢ… ሁለት ነገር በአንድ ግዜ ሆኗል:: ረቂቅ ስራው አይመረመርም! በአካልም በስልም ተገኝታችሁ መላው ቤተሰቧን ላፅናናችሁ ሁሉ ምስጋናችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ!