ለአክአብ ተገለጥ!

0
627

ቤተክርስቲያናት ምእመናቸውን ይዘው ሲፈልጉ ምህላ፥ ፆምና ሱባኤ እያወጁ፤ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ እየናጠ ያለው የውስጥ የበዳይ ተበዳይ የዘር እና ሃይማኖት ቁርሾ ባላየ እንዳልሰማ ሆነው፤ ከራሳቸው አልፈው እግዚአብሄርን ሊያታልሉ ሲገበዙ ግዜ ጠብቆ የተጠመደ ቦንብ እየፈነዳ ፀሎቱም ምህላው ከሰማይ መልስንም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነትንም ማስገኘቱ ቀርቷል፤ ሰማያት ተዘግተዋልና! ቤተክርስቲያን ባላየና ባልሰማ ሰውን ከማታለል አልፋ እግዜሩንም ልታታልል ስትጥር አቅምና ጉልበቷ የነበረው ፀሎቷ እጅግ ማድረግ አቅቶት የነበራትን ብቸኛ ኃይል አጥታለች::

ኃይሏንና ክብሯን የወሰደባት ደግሞ ኮረብታማ ነገር ስታይ ከክብሩ ቀኝ ካስቀመጣት ስፍራ ሸርተት እያለች ብቻዋን ያለ ባሏ ልታይ ልታይ እንድትል የሚያደርጋት አስጢናዊ ባህርይዋ ያደገባት ስለሆነ ነው:: ፀሎትና ምልጃዋ ማለትም እጣንና ሽቱ የተሰጣትን ይዛ ሄዳ ቤተ መንግስት ውስጥ ከሰል የምታነድ ስለሆነች ነው::…….”የሰማይን መንግስት ተጠባበቂ” “እመጣለሁ” “የኔ መንግስት ከዚህ አይደለም” የሚሉ ብዙ ብዙ ደብዳቤዎች እና መልእክቶች አሉ ባሏ የሚላት:: ነገር ግን እርሷ ከልጅነቷም አታላይና ወስላታ ሚስት ሆና ውሽሞችን አብዝታለች:: ከሄደ ከመጣው መንግስት ጋር ሁሉ ጋር. አደባባይ ወጥታ ትጣቀሳለች!

የአደባባይ ሚስጥር የሆነው ቤተ እምነቶች ባጠቃላይ ጓዛቸውን ጠቅልለው መንግስት ቤት መግባታቸውና ፀሎታቸው ይሁን ምህላቸው፥ ፆሙ ይሁን ፀሎቱ፥ ውግዘታቸው ይሁን እቀባቸው በመንግስት ተቃኝቶና ተፈቅዶ ሲያበቃ ነው ወደ እግዜሩ በምእመኑ እንዲደርሰው አማኞችንም በቃል ባለ አቋም ሳይሆን በbrainwashing tactic “ለበላይ ተገዛ” ይላል ቃሉ በሚል ጭፍን አስተምሮ ህዝቡን ያስታሉ:: ልክ ለበላይ ተቀማጮች condition set ያላደረገ ይመስል:: ቃሉ በበታች ያለን እንድንገዛ የሚያዘን በበላይ ያለው ገዥም እንደቃሉ ካስካላስጨነቀና እስካላስቆጣ ድረስ ብቻ ነው::

“እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው”ኤፌሶን 6:9

“ጌቶች ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና ለባሪያዎቻችሁ በጽድቅና በቅንነት አድርጉላቸው። ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ።” ቆላሲየአስ 4:1

እዚሁ ፌስቡክ ላይ ጨምሮ በቤተ እምነት የሚነገረውና የሚሰበከው ለእኛ ብቻ ለበላይ የመገዛት ጫና እንዳለብን ነው:: ሆኖም የእግዚአብሄር ቃል ግን ለበላዮችም ያስቀመጠው መስፈርት አለው:: መንግስት እነኝህን መስፈርቶች እስካሟላ ነው ህዝበ ክርስቲያኑም ሊገዛለት የሚችለው:: በመፅሃፍ ቅዱሳዊ እውነት ስንገዛ የበላዮችም በመፅሃፍ ቅዱሳዊው ስልጣን ቃል ስር እስከተገኙ ነው::

አሁን ግን አገራችንን የሚንጠው ችግር በቀላሉ በምህላና ፀሎት ሱባኤያችን ያልተመለሰበት ምክኒያት አገሪቱን የናጠ ያለው የዘር ቁርሾ ቋት በክርስቶስ ባልነው ቤት ውስጥ ሃሳቡ መስተናገድ ብቻ ሳይሆን ስፍራ አግኝቶ እየተተገበረ በመሆኑ ነው! የእገሌ ዘር አይፀድቅም ከሚል ምፀት እስከ “የእንትና ነፃ አውጪዎች” ነን ባዮች፥ በክርስቶስ እንኳን ነፃ ያልወጡ ነፃ አውጪነትን ሲገበዙበት፤ በቤተ ክርስቲያን ጥንስሱን ጠምቀው ለመጠጣት በቅቶ መንክራትና ፓስተራትን ስላሳከረ ነው::

ጠንሳሾችና በዚህ የጥላቻ ጉሽ ጠላ የሰከሩ ባለካባና ቆብ ፤ የተለሰኑ መቃብሮች ቅራሪያቸው ለልጅ ልጅ ሊተርፍ በየመቅደሱ ቅድስትና መድረክ ላይ ጠላውን እየተጎነጨ ቋሚ ስለበዛ ነው:: ከማሰሮው ሳይጎነጭና ሳይስማማ በጠልተኝነት ጠላ ካልተሳከረ መድረኩስ የት ተገኝቶ::

ዛሬ ፆምና ፀሎት ቢታወጅ ምህላና ውግዘት ብናደርግ ሱባኤ ሲታወጅ ፀሎታችን እጅግ ማድረግ ሲያቅተው እንደ ፃድቅ ሰው ያለ ፀሎት ባለመፀለያችን መሆኑን ተገንዝበን መጀመሪያ ራሳችንን ውስጣችንን እናንፃ!

ክፉ ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርገው ነገር ሲሆን ቶሎ የሚያስቆጣም የሚያስደነግጠውም ህዝቡን እንጂ ሃይማኖት መሪዎችን አይደለም:: እነርሱ የህዝቡን የቁጣ ግለት ለክተው በዛው ልክ ሰፍተው የሆነ የሆነ ቃል ወርወር አድርገው ለይስሙላ ይማተባል ይፀለያል ይዘመራል ይዘለላል:: የመሪዎች ጩኸት ግለት በመለካት ስለሆነ ህዝቡም አሁን አሁን ከእነርሱ መስማትም ትቶታል:: ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ቀውስን ፈጥሯል:: አደገኛ ነው!

በእምነት ቤት ላይ በመሪነት የተሰየሙ ሰዎች ጩኸት ሊሰማ ያልቻለው እነርሱ ከአክአባዊው መንግስት ጋር ተዳብለው ለበኦል እየሰገዱ ስለሆነ ነው:: የነኤልዛቤልን ዛቻ ፈርተው በሌላ ቀንበር ሊያዙ ጎንበስ ያሉና ቆባቸውን ያወለቁ ሆድ አምላኩዎች ስለሆኑ ቤተክርስቲያን ሃይሏን አጥታለች:: ለባቢሎናዊቷ መንግስት ለጠፈሯ ንግስት ቂጣ ጋጋሪዎች የባቢሎን ምርኮኞች ስለሆኑ ነው:: ንጉሳቸውን ትተው ኬክ ጋግረንላት ርሃብ የምታርቅልን ቂጣ ጠፍጥፈንላት ሁሉን የምታስገዛልን እጣን አንቦቅልቀን በግብዣዎቿ ፊት ወንበር የምታሰጠንን ምድራዊቷን መንግስት እንፈልጋለን ስላሉ ነው:: “አባታችን ሆይ”ን ትተው “እናታችን ሆይ በምድር ያለሽው ከስልጣንሽ አቋድሽን የለት እለት እንጀራችንን ስጪን” እያሉ ለmystery Babylon ጎንበስ ቀና ስለሚሉ ነው::

በእውነተኛ በእግዚአብሄር መንፈስ የሚነዱን ሰዎች ይህንን የጥፋት ተባባሪ ጠላ ጠማቂነቷን የተቃወሙ እና ለባኦል አንሰግድም ያሉ ደግሞ ግዞተኞች ሆነዋል:: በብዙ መከራና ስደት ርሃብና ጥማት ሲያልፉ፤ የቤተክርስቲያን ላይ ተሹመው ቆብ ደፊ ፓስተራት መንክራት ግን በብዙ ሚሊየን ብር በሚያወጣ መኪናዎች ሲንፈላሰሱ….. ሱፍና ቀሚሳቸውን በመልክና ባይነት በዲዛይነሮች ሲያሰፉ ለአክአብ ወንበር አሟቂዎች ሲደረጉ ለባኦል አንሰግድም ያሉቱን ግን በሰይፍ ስለት አብራ አስጨፍጭፋለች::

መንግስት የቤተክርስቲያንንም ክብር ደርቦ መጎናፀፍ ፈልጎ በዚህ በኩል “ካውንስል” በሚል ስም በዚያ ደሞ “እርቅ” በሚል ስም ወደራሱ አምጥቶ በቤተ መቅደስ እቃ የሚጠጣና የሚሳከር ሆኗል:: በመቅደስ ጠላውን ሲጠጡ የለመዱ ደግሞ ቤተመንግስት ገብተው ሲጎንጩት ለእነርሱ ክብር እንደሆነላቸው ሁሉ ታብየዋል:: አብይን እንደ መሲህ ማቆላመጥን ተያይዘውታል::

የናቡቴን እርሻ ሲወስድ ዝም ብለዋል:: የፈለግሁትን ሳደርግና የናቡቴን የአባቶቹን ርስት እወስዳለሁ ስል ተው ከተባልኩኝ አልጋዬ ላይ ተኝቼ አለቅሳለሁ የሚል ህፃንን ንጉስ በነኤልዛቤልና በባኦል ነብያትነት በገቡ የቤተክርስቲያንን ክብር በሸጡ የእመነት ቤቶች መሪዎች ተው ባይነት ሳያገኝ ህፃኑን ንጉስ አክአብን እሹሩሩ ይላሉ:: ናቡቴ እርሻውን እንዲቀማ ሲደረግ፥ ቤቱ ሲቃጠል፥…….”ናቡቴም አክዓብን፡— የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ።” ስላለ በደለኛ ሲደረግ ዝም ይላሉ፥ የግፍን ደም ምድር ስትጠጣ መኃል እንደ ካህንነታቸው ገብተው ይህ ነገር ልክ አይደለም ማለት ያልቻሉ ……ኃይለ ቢሷ ቤተክርስቲያን ጥግ ይዛ ባላየ ታልፋለች::

ህዝብ አምላክ እንደሌለው ሰሪው እንዳላበጀው እየተገፈተረ በሻሸመኔ፥ ዝዋይ፥ አሩሲ፥ በጉራፈርዳ፥ ጊምቢ፥ ቡራዩ፥ ለገጣፎ ፥ ቤኒሻንጉል ሰው እነ ቆሎ ሲረግፍ እርሻው ሲወሰድ፥ ቤቱ ሲቃጠል ፥ አንገቱ በካራ ሲታረድ፥ ቤተክርስቲያን ባላየ እያለፈች ናቡቴን ጥፋተኛ እያደረገች ይልቁን ለመንግስት ልታረጋጋ መኃል የምትገባ የገዢዎች ልዝብ በትር ሆናለች:: የናቡቴ ሞት ግፍ ነው እንዳትል ስም ስታወጣና ስትፈላሰፍ ያለፍርድ ደም ከመንግስት እጅ እያስታጠበች ታደርቃለች:: ጮኻ የለም ይሄ “የናቡቴ እርሻ ነው ግፍ ነው” እንዳትል የአክአብ ሎሌ ሆናለችና!

ሰማይን የዘጋ ምናልባት የጥቂቶች ለአክ አብ ያልሰገዱ ቅሬታዎች የነኤልያስ ጩኸት ይሆንን? ምን ይመስልሻል ቤተ ክርስቲያን?

ከመንግስት ጉያ ውጪና የራስሽን የብቻ ድግስ አቁሚና ወደ መኃል ጥናውን ውስጂ እሳቱን እጣኑን ጨምሪና ይዘሽ ወደ ህዝቡ መኃል ሮጠሽ ግቢ! ይህንን መቅሰፍት አስቁሚ! ስለህዝብ ተማፀኚ! ስብከት መድረክ ማሞቂያ የማድረግሽን ግድፈት ተይ! ካህናቶችሽን በህዝብና በፈርኦን መሃል አግቢ!

በህግ ለተገባች ውሽምነት ያስጠላል! እንደ ተተውችና እንዳልተፈገች ሆነሽ፤ ካየሽው ሁሉ ጋር እንደ ሜዳ አህያ የፍትወቷ ግዜ እንደደረሰ መሆኑን ተይ ይልሻል ጌታሽ! ተይ! ቤተ መቅደሱም ሊፈርስ ህዝብም በግዞት ባቢሎን ሊወርድ ነው! ተይ! ንቂ!

ዛሬ “ጴንጤው” ንጉስሽ ጦር ሲሰብቅ ልጆችሽ ደግሞ በጥራዝ ነጠቅነት ያሳደግሻቸው ያንቺን ቅራሪ ዞር ስትይ ፉት እያሉ ያደጉቱ፤ በየፌስቡኩ ቃል ከእግዚአብሄር እየሰረቁ ዝም ብሎ መረገጥ ነው፥ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ይህች ነች፤ እያሉ ለፍትህ የመጮህ አቅም የሌላቸው አቅመ ሰላላ ሆነዋል:: ፅድቅን መስበክ የማይችሉ ጉልበታቸው ባንቺው ጉሽ ጠላ የላላባቸው፤ አለምን በራሷ አልባስ መብራትና ጭስ ሊያስገርሟት ዜማ የሚሰርቋት አጓጉል ሆነዋል:: ትምህርቷን ኮርጀው በእግዚአብሄር ቃል አሽተው ሊያመናፍሱ ከባቢሎንን ከሩቅ እሩቅ ምስራቅ አምጥተው አሜንን እያሳከሉ ይተርካሉ::

ቤተክርስቲያን ሆይ:- የምትደልይው ሲልሽ በቀብድ የምታሲይዠው ይህ ህዝብ አምላክ አለው:: እድል ፈታዬ ነው የሚለው አምላክ አለው! ጭራሹኝ በግዞት ከእጅሽ አውጥቶ ሊያስማርክ ካለው ጥፋት ቶሎ ካለሽበት የመንግስት መደብ ተነስተሽ አቧራሽን አራግፈሽ ወደ ስፍራሽ ተመለሽ:: ዛሬውኑ እስራትሽን ከመንግስት የተዋደቅሽበትን ገመድ ከአንገትሽ ፈትተሽ ወደ ቦታሽ ተመለሽ! ከመንግስት አልጋ ውስጥ ውጪ! ወደ ክብርሽ ዙፋን በሰው ወደ ተናቀ በእግዚአብሄር ግን በከበረው የማእዘን እራስ ወደ ተመሰረትሽበት ድንጋይ ቶሎ ተመለሽ! ሙሽራ ያለ ጌጧ ድሮም ማስጠላት እንጂ ውበት አይሆንላትም! ሚስት ውሽምነት ስትገባ ነውር ነው!

ኮብልይ! ሮጠሽ ቶሎ ውጪ! መንጋውን አስመልጪ! በአንቺ ውስልትና መንገድሽን ለተማሩ ሁሉ ምሳሌ ትሆኚ ዘንድ ምናባት ከጥፋት ማምለጥ ቢሆንልሽ፤ ከባቢሎን ልጅ ጋር የተቀመጥሽ የፂሆን ልጅ ሆይ ኮብልይ!

የጦርን አታሞ የሚመታውን ህፃኑን ንጉስ አክአብን ተው በይው! ታሪክሽ አብሮ ጎዳፊ ነው! ገፅታውን ባንቺ ገንብቷልና!

ስለ ለናቡቴ ጩሂ! ለአክአብ ተገለጪ! ይህ አይደረግም በይ!

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን።

ሊዲያ ዘውዱ