የልባችንን ጣኦታቶች እንቀለጣጥም

0
222

“ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።” 1ኛ ዮሃንስ 5:21

ጣኦት ግን ምንድን ነው?

አንድ ነገር ጣኦት መሆን ሚጀምረው ለአንድ አማልክት ትልቅ ግንብና ቤት በመስራት አይደለም! ጣኦት ማምለክ የሚጀምረው እግዚአብሄርን እንደ እግዚአብሄርነቱ ሳናመልከውና ከቃሉ ውጪ በሆኑ ልምምዶች ልናመልከው ስንፈልግ ነው:: ቃሉ ከሚገልጠው ውጪና ፥ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ያጋነን ሲመስለን እንተላለፋለን! ለዚህ ነው ናዳብና አብድዮ የእግዚአብሄር እሳት የበላቸው:: ከህግ ትዛዙ በላይ ለ”በአሉ ድምቀት” በሚል ይመስላል እንግዳ እሳት ይዘው መጡ::

“የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ።

እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ።” ዘለዋዊያን 10:1-2

ናዳብና አብድዮ ሌላ አምላክ አላቆሙም:: ወደ ሌላ አምላክም ቤት አልሄዱም:: ግን እግዚአብሄርን በትእዛዝና በቃሉ መሰረት አልቀረቡትምና ፥ ከሌላ ስፍራ ከባህልና ወግ ትምህርታቸው አምጥተው በእግዚአብሄር ፊት እንግዳን እሳት ሊያነዱ ሲገበዙ ከእግዚያብሄር ፊት ግን ሌላ እሳት ወጥቶ በላቸው! እግዚብሄርን ሊያሻሽሉት ትእዛዚቱን modify ሊያደርጉ አለልክ ሲቀኑ ፥ የራሳቸውን ፅድቅ ሊያቆሙ ደፋ ቀና ሲሉ ወደቁ! እንዲህ እንድሁ እያለ ይጀምርና ፈፅሞ ሌላ መንፈስ ማስተናገድ ይጀመራል ማለት ነው:: ከዚያ እስራኤል እንዳደረገች አምላክዋን “ባኦል” ብላ አምላኳን መጥራት ጀመረች! ”በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤” ሆሴእ 2:1

This is how Isreal began to confuse their Elohim Yah with other Gods. However, this slippery slope began to divert Israel from the Holy living Word!

ሌላው ጣኦት ጌታን እናመልካለን እያልንም ጣኦት በልባችን ሊነግስ ይችላል::

” በፍፁም ነፍስህ ፥በፍፁም ሃሳብህ ፥ በፍፁም ልብህ እግዚአብሄርን ውደድ” ማቴዎስ 22:37

ልባችን ላይ የነገሰ ፥ ፍፁም ሃሳባችንን የያዘ ፥ ያምኞት ቢሆን በፀሎት መልክም እያሸነው በጣም የፈለግነው ነገር እርሱ ጣኦት ነው:: በልብና ሃሳብ ላይ በፍፁም ነፍሳችን የሚነግስብን ሁሉ ጣኦት ነው::

ይሄኛው ጣኦት ደግሞ ሽፋኑ የሃይማኖታዊ ቅናት ነው:: ጳውሎስ በዚህ በሽታ ይሰቃይ ነበር:: ”ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።” ፊሊጲሲዮስ 3:6 ይላል ጳውሎስ እራሱን በትዝታ ፈረስ የኋሊት እያየ::

ለምኩራቢቱና ለህጉ ከልክ በላይ እየቀና የጌታን ሃዋሪያትን ሁሉ ማሳደድና ብሎም እስከ ግድያ ትብብር አድርሶታል:: እስጢፋኖስ ሲገደል እርሱ አሯሩጦ ማስያዝ ብቻ ሳይሆን እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ጳውሎስ ቆሞ ልብሱን ይዞ ያይ ነበር:: ጌታም ተገልጦ

“በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፡— ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ።ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፡— አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል፡ አለው።” ሃዋሪያት ስራ 9:4

ይህ ሰው የሚያድነው ቃሉን ወይንም ጌታን ሳይሆን ሃይማኖታዊ ወጉና ስርአቱን ለማስቀጠል ያለልክ ሲቀና የእውነትን መንገድ ተላልፏት ነበር:: ሃይማኖቱ ከሚያድነው ከክርስቶስ በላይ ጣኦት ሆኖበት ነበርና! ጳውሎስ እኮ እጅግ የተማረ ፥ በገማሊያ እግርስ ስር ሆኖ ቀኖና በጥብጦ የጠጣ ፥ በህግም ብትጠይቁት ያለነቀፋ የነበር ሰው ነው:: ቢሆንም ይህ ሁሉ እውቀት መፅሃፍ የሚተርክለትን መሲሁን የእውነትን ጌታ ክርስቶስ የሱስን አልገለጠለትም ነበር:: እንዳውም ተደፍኖበት አሳዳጅ ነበር:: ለምን? በፍፁም ልቡ ፥ በፍፁም ሃሳቡ ፥ በፍፁም ነፍሱ ሃይማኖቱ ነግሶበት ነበርና::

ወዳጆች ከጣኦታት እንራቅ! ውስጣችንን እናፅዳ! ተራፊም የሰራንላቸውን ሃሳቦችና ምኞቶች አፀዶችን ዛሬ ከልባችን እናፍርስና እንቀለጣጥም! መቅደሱን አንውደድ ከመቅደሱ ጌታ በላይ:: ከተሰዋው ይልቅ መሰዊያውን አናስበልጥ:: ከእግዚአብሄር ቃል በላይ ለወግና ስርአታችንን ጠብ እርግፍ አንበል! ጥንታዊነታችንን የፅድቅ ምልክት አናድርገው:: ሰይጣንም የሰይጣን አምልኮም ጥንታዊ ነውና! ጥንታዊነት በራሱ ፅድቅን አያመላክትም! ጥንትም ጣኦታትና አማልክቶች ነበሩና! መጠነቱንማ ከባቢሎን በላይ ላሳር እኮ ነው! ሰይጣን በኤደን ገነት በራፍ ቆሞ ሲወሸክት ፥ የቅጠልን ግልድም ለአዳም ሲያስለብስ የባህል ልብስ የሚል ወግ አስጀመረው ማለት እኮ ነው:: አዳም አልቆለት ነበር ጌታ ምህረቱንና እውነቱን ፥ ፅድቁንና ፍርዱን እያገናኜ ጣልቃ እየገባ ባይመራው:: ቅጠሉን ገፎ ቆዳ ባያለብሰው ሃፍረቱን እንደታየ በኖረ ነበረ ቅጠል ይሸፍንለት ዘንድ አይችልም ነበርና:: እዛችው ዛፍ ስር ተደብቆና ተሸማቅቆ በቀረም ነበር::

ሌላው በጠልሰም ፥ በስእል መልክ ፥ ክታብ መልክ ፥ በሰው እጅ በወርቅ ፥ በብር ፥ በእንጨት የተሰራ ነገር ሁሉ አምላክን መመሰል ነው:: እስራኤል በዚህ ጉዳይ በጣም ይበድል ነበር:: በምድረ በዳ እባብ ሲነድፋቸው እባብ ተሰቅሎ በምሳሌም የነገር ጥላ ሆኖ እንደዳኑ ፈጥነው ረስተው ያንን እባብ ማምለክ ጀመሩ! በእውነትና መንፈስ የሚመለክን አምላክ በአራት እግር ባላቸው በእንስሳ በእጅ በተሰራ ነገር መለወጥ አበዙ::

”በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፥ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው።በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ።” መፅሃፈ ነገስ ካልእ 18:4

ዛሬ ልባችን ላይ የገዘፈውን ሃሳብና ምኞት መመኜትና ቅንአት አስወግድልን ብለን ፥ እንለምን:: እርምጃም እንውስውድና እየጎተትን ከመቅደሱ ማለት ከልባችን ፥ ከማደሪያው ከሰውነታችንን ጣኦት የሆነብንን ምኞትና ፥ ፍላጎት ፥ ቅንአትና ትምክህት እናስወግድ::

ጣኦታትን ቀለጣጥሙ!
Crush the idols!

የጌታ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

ሊዲያ ዘውዱ