እስከመቼ?!

0
252

ኮሮናን አጥፋ ብለን ስለኮሮና ስንል ንስኃ እንዳንገባ ብዬ እፈራለሁ በልቤም ብዙ ጭንቀትም አለ !

አደራ ንስኃችን ስለበደልነው ጌታ ይሁን! እስትንፋሱን ሰጥቶን የምንኖር እኛ ብዙ ምፀት ስናሰማ ገሚሶች በአይናችን ፊት መልካም የመሰለንን ሁሉ በዘፈቀደ ስንሰራ “ኃጥህ ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም”ና ፥ ግማሾች ባበጃጃት በሰራት ምድር ላይ እየተራመድን እስትንፋሱንም ተበድረን ሳለ ከናካቴው መኖሩንም ስንክድ ፥ ከፊሎች ደግሞ እራሳችንን ጥቃቅን አምላኮች ስናደርግ ፥ የቀረነውም ቃሉን ስንሰርቅና ለክፋታችን መሸፈኛ ስናደርግ ብዙ ብዙ ስንሆን ታይተናል! በተሰጠን እስትንፋስ “ለሰማይና ምድር ጌታ መዋል ማደር መለየት በፅድቅ መሰደድ ትርፍ የለውም” ብለን አገልግሎታችንን የናቅን በኃጥእ የቀናን ነን:: አብላጮች ደግሞ ቃሉን እንኳን የማናነብብ ለቃሉ የማንገዛ ግን በሃይማኖት አለኝ የምንኮፈስ ግብዞች የሆነን ጌታ ህይወቱን እንደሰጠን የማናቅ የሰዎች ሃይማኖት ተቋማትን በአገራችን ባመጣንበት እድሜ ብልጫ አንዱን የምናፀድቅና አንዱን የምንኮንን ነን ዳሩ ሁሉም ከባህር ማዶ ቢሆንም ግኝታቸው:: አንዱን አገር በቀል አንዱን ልውጥ ለማድረግ የምንታትር ስለ መቅደሱ ጌታ ሳይገደን በመቅደስ የምንጣላ ነን! ሌሎችም በጌታ ቤት የኖርንባቸውን ዘመናት ስናስቆጥር በዘመርነው መዝሙር ብዛትና ስብከት በራሳችን ስራ የምናፀድቅ አለን:: ረጅም እድሜ ጌታ ቤት ማስቆጠራችን ልማድ ብቻ ሆኖብን አየቀደመውን ፍቅር ያስጣለን ሆነናል! አያሌ መፅሃፍትን በሰዎች የተፃፉ ለእውነተኝነታቸው እንኳ ምንም ማረጋገጫ ሳንይዝ ባዶ አእምሮዋችንን ልንሞላና አዋቂዎች ተብለን ልንታይባቸው ሰባ የሞተ ፈላስፋ ጥቅስ ስንመዝዝ አንቱ ልንባል መደርደሪያ የሞላን ነን:: ነገር ግን ህያው የሆነ ቃሉ ቸል ስንል እርሱም ቸል ሲለን መልሰን ያንኑ የጥፋት ሁኔታችንን እንደሌለ ማሳያና ማመሳከሪያ ስናደርግ በራሳችን ሃሳብ ዋዥቀን መሪ እንደሌላት መርከብ አቅጥጫ ቢስ ሆነን ስንጠፋ በማአበል እንግልት የደረስንበትን ስፍራ ላይ ሆነን እንኳ ገና የማናስተውል እንደጠፋን ያልገባን የደረስንበትን ዝቅጠት ስናመናፍስና ስናፈላስፍ አዙሪት ናላችን ያዞረብን ነን::

“እናንተም፡— እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል? አሁንም የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዓን ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ጸንተዋል እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም፡ ብላችኋል” ሚልክያ 3:17

ቸነፈር ሲመጣ ግን ደርሶ እጁ ዛሬም ከማዳን እንዳላጠረች የሚበራልን ፥ ምድር ስትከፋ ርሃብ ሲጠራ ግን ጆሮው ከመስማት እንደማትደነቁር የሚታየን ፥ በምርኮ ስንበዘበዝ ሱባኤ የምንይዝ ፥ አባይን እንደ ቀይ ባህር ልንከፍል እምነት የሚሆንልን ፥ አለም በሃጢያት ረክሳ ከእግዚአብሄር ቤት እንኳ ጆሮን ጭው የሚያደርገው እርክሰት ሲወጣ ያላስለቀሰን ለወረረሽኝ ፀሎታችንን እንደ እጣን ስናሳርግ እግዚኦ ያ ይመጣል ያሉት ዘመን መጥቶብናል ማንስ ከዚህ ይሰውረናል ያስብላል! እጣኑንም ወስደን ለኮሮና ለባለዘውዱ ወረርሽኝ ጣኦት ስናቆም ደሞ ገና ስናጥንለት ቁጣውን የምንቆሰቁስ ሆነን ነው:: ድሃ ቤቱ ሲፈርስ ለሽ ብለን የምንተኛ ፓስተሮች ቄሶች አገልጋዮች ዛሬ ኮሮና ነፍስ ስጋችንን አለያይቶ “አገልጋዮች የቤት ኪራይ የሚከፍሉት የለም ብር ይሰብሰብ” እንላለን:: ለመበለቲቱ ሳንፈርድ እንዲያም በትንቢት ስም አታለን የቤቷን ካርታ የወሰድን ሃሰተኛ ሰብስኪዎች አንዴ ኮሮናን በእጄ ጨብ አድርጌ አጠፋለሁ ሲሉን ፥ አንዴም እጣን ሲያጥኑልን የኛውን ድካም የእኛን እረኛችንን ድምፅ ያለመለየት ፍየልነትን ያሳያል:: ሃጢያተኛይቱን ከተማ እጣኑን ወስደን አጠንላት ከነኃጢያቷ ልናፀድቃት መሆኑ ነው እንግዲህ:: እሱም “በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ምልክያ 1:10 ይላል::

መልሰንም በእኔ ፀሎት ሰምሯል ነገሩ ልንል ለመረባችን የምንሰዋ ሆነናል:: ለእጣናችን ስንሰግድ መሆኑ ነው:: አቤት መድረኩን ለመቆጣጠር ያለው ሽሚያ! መልእክት የሌላቸው መልእክተኞች! “ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል” እንባቆም 1:16

እውቀት ከካህኑ አፍ ሲጠፋ እኛም ቃሉን ሳይሆን ነብያትን ከልባቸው እያወጡ ከየትም ያምጡት የሚሰጡንን ትንቢት ስንሰማ በመረብ ተይዘን ቃሉን ሳይሆን ለችግራችን መላ ብቻ ስንፈልግ ነው:: “ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል” ሚልክያ 2:7

ሰው ቢኖርበት ህይወት የሚሰጥን ህያው ቃሉን በወግ ያልተማረን ሰው ከብቦ በአጋንታዊ ምትሃት በመሰለ እንቅስቃሴዎች ካሜራ ደግኖ ፈሪሃ እግዚስብሄርን ከምድር ገፅ ሊያጠፉ ትውልዱን ሲበድሉ ጎንበስ ቀና ሲሉ ይውላሉ! ቸለል ስንለው ቸል በተባልን ደግሞ ይባስ ብለን ዛሬም እንዳንመለስና እንዳንፈወስ ሱባኤውን ለኮሮና ፥ እጣኑን ለግድብ ፥ በመመለስ ፈንታ ጌታ እራሱ መጥቶ በሪቫይቫል እንዲያነቃቃን የተደበርንበት ሆነናል:: ”በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ።” ሶፎንያስ 1:9 የምንፈልገው ያ የሪቫይቫል ቀን እኮ እንዲህ በዋዛ አይመጣም:: አንጥረኛ ብርን እንደሚያነጥር ሰው የሚያነጥርበት ቀን ነው ያ ቀን! “ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥” ሶፎንያስ 1:15 ማን ይችላታልና ነው ዛሬ ሳንነፃ ፥ ሳንቀደስ ፥ ፊታችንን ሳንመልስ ፥ ቅሚያ የሞላብን ሆነን ሳለን የመቅደሱን ጌታ ና የምንለው ምሁነን ነው?

አሁንም እንደ እግዚአብሄርነቱ መጠን ባናከብረውና የመዳንን ራስ የሱስ ክርስቶስን ቸል ብለን የቃላት ውጊያ ገብተን ዘላለማዊ ክህነቱን “አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ ከራሱ የሚበልጥ ቢያጣ በቅዱስነቱ አብ የማለበትን ያንን መኃላ ስንሰርዝ ስደልዝ ለራሳችን ማእረግ ፈልገን እኛ በሰዎች ላይ አምላክ ልንሆን ስንገበዝ አይደለምን? ከጌታ ይልቅ ለተቋማን ስንሟሟት አይደለም ውይ?

በኩር ሆኖ የመላእክትን ዘር ሳይሆን የኛን ስጋ ለብሶ ፥ በትንሳኤ አንስቶ ፥ ሰው ሆኖ አርጎ ወደ ሰማይ በወንድሞች መካከል በኩር ሆኖ በቀኜ ተቀመጥ ያለው ዛሬ የምስጋና ዘውድ የተጫነለት የነገስታት ንጉስ ተብሎ የጌቶች ጌታ ከብሮ ፤ ከስሞች ሁሉ በላይ ስሙ ከፍ ሲያደግለት አባቱ ከስልጣናት ከኃይላትና ከጌትነት በላይ ብሎም ሊመጣ ባለው አለም ሁሉ ስሙን ብቻውን አግንኖለት ሁሉን ያስገዛለት የሰው ልጅ በአባቱ ክብር የከበረው ፤ እኩል ሲሆን መተካከልን ከመቀማት ሳይቆጥር በእኛ ስጋ ምሳሌ ትንሳኤን አንስቶ ዘላለሙን እንደዚህ ሆኖ ሊኖር ፈቅዶ ነው! “በታላቅም ድምፅ፡— የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል፡ አሉ” ራእይ 5:12 እየተባለ ከፍ ያለውን ደርሰው የእፉኝት ልጆች የሆኑ ይህንን ክብሩን የሚክዱና ዳግም ይመጣል እንዳይሉት ተናንቋቸው ንስሃቸውን ምትሃታዊ ለሆነ ቫይረስ ያደረጉ ያስደረጉ ሃሰተኞች ብዙ ናቸው:: ቫይረስ ከሚል ጀርባ ያለውን ሰይጣናዊ ሴራ እንኳን ማየት የተሳናቸው ሰዎች ናቸው:: ቤተክርስቲያን መሪዎች ሲባሉ ባለሙያ ሆነው ተኩላ ሲያዮ በግ ጥለው የሚሸሹ ቁጥር የላቸውም ዛሬ:: በጎችን ወደ ጨለማ የሚነዱ ቅጥረኛነታቸው እራሱን ስራቸው ሲያሳብቅባቸው እፍረትን የማያውቁ ሆነው ነው! ሊገለጥ ካለው ቁጣ ልንሸሽ አይኖቻችንንም ተመልሶ ዳግም መጥቶ የሚወስደንን ሙሽራ እንዳይጠባበቁ የሰርግ ልብስ ሳንለብስ ኩሉን ሳንቀባ በእድፋም ልብስ እንደለበስን “ቃል አውጣልኝ ቃል አግባልኝ” “ላውጅባችሁ?” “ዘይት ግዛ መሃረብ” “በመቁጠሪያ ጀርባህን ተደብደብ” “በካራቴ ሰይጣን ላውጣ” ከሚሉን የጥልቁን ፓስተራትና መንክራት ያንከራትቱናል የበጎች እረኛ የሆነውን የነፍሳችንን መድሃኒት አንሰማ ስላልን ነው::

“ብትወዱኝስ ትዛዜን ጠብቁ” ጌታ የሱስ ክርስቶስ (ምናልባት እንደዚህ ከገባን ብዬ ነው )

ወገን! በዋኖሶችና በእርግብ በኮርማና በጠቦት ደም እኮ አይደለም የተዋጀነው! መድኃኒታችን የሱስ ክርስቶስ በከበረው በገዛ ራሱ በዘላለም ኪዳን ደም ነው የዋጀን! እና እራሱን መባና መስዋእትና የመአዛ ሽታ አድርጎ የኔን ስጋ ለብሶ ስጋዬንም አንፅቶ ፤ በሰማያት ለእኔ መዳን በኔው ስጋ በኩር ሆኖ እኛ ታናናሽ ወንድሞች ልንደረግ አልፎ በሰማያዊቷ ድንኳን ሲገባ ይህ ድንቅ በዘላለም ዘላለማት መካከል የመጀመሪያ ክስተት ሰው የሆነው ክርስቶስ የሱስ ወደ ሰማያት የገባ ቀን ነው! የጥልን ግድግዳ የፈረሰበት ቀን! ሰው በሰማያት ያለ እድፍ ያለነቀፋ ሆኖ በክብሩ መንበር በምሳሌው የተገኘበት ቀን ነው! የነበረውን ትልቅ ድግስና ሰማያዊ ፌሽታ ማሰብ ነው እንግዲህ! አባቱም ልጁን በብዙ ወንድሞቹ (በእኛ) መካከል በኩር ሆኖለት መጣ! እኛ ሁሉ በክርስቶስ የሱስ በተቀባው አዳኝ ውስጥ ተሰውረን ታየን! ለፊተኛው አዳም ጥፋት የሁለተኛው አዳም ማዳን ጌታ የጠፋውን በግ ያስገኘው እንዲህ ባለ ድንቅ ስራ ነው:: “ስራህ ግሩምና ድንቅ ነው በሉት” አርነታችንም እንዲህ በደም ተዋጀ! አብም “ና ታዛዡ ልጄ ሃጢያትን ያልነካ በነገር ሁሉ እንደ አዳም ተፈትኖ ፊተኛው መታዝዝን ትቶ ሲወድቅ ኃለኛው ታዝዞ ከዛች ፍሬ “ድንጋዮን ዳቦ አድርገው” ሲባል “ሰው በእግዚአብሄር ቃል እንጂ በእንጀራ አይኖርም” ብሎ ያችን የሞት ፍሬ ያልተቋደስከው የመስቀልን ሞት እንኳ የታገስከው …አንተ የምወድህ ልጄ ና በቄኜ ተቀመጥ ያለው ደሞም የምስጋናን ዘውድ ጭኖ ሁሉን ያስገዛለት፤ ልጁም ሁሉን ላስገዛለት በፍቃዱ የተገዛለት በመታዘዝ ከፍታውን ያገኘ መቀማት አልሆነበትምና ….

እናም አብ አባት አሁን ዞር ሲል በስጋ ያረገውን በመለኮት አምላክ የሆነው የሱስን አይቶ ነው መማለዳችን መዳናችን ዋርሳነታችን ቤዛነታችን!

መማለድ ስንባል “እባክህ እባክህ ተው ተው ግን እባክህ ግን ተው አፅድቃቸው ግን ተው ” ተብሎ የሚለምንን አይነት እኮ አይደለም! ምልጃ! ብዙዎች ያልተፈታላችው ይህ ምልጃ የሚለው የአሰራር ትርጉም ነው:: የምኩራቧን ስርአት ማጥናት ለበለጠ መረዳት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው! ምልጃ በደም ነው የሚደረገው:: ደሙን ያፈሰሰ ከጌታን በቀር እንዲህ ማን ነው?

በአይሁድ ስርአት ሊቀ ካህናቱ ወደ ድንኳኒቱ ሲገባ የኮርማ ደም ይዞ ሲሆን ፤ አንድም ለራሱ ኃላም ለህዝቡ ኃጢያት ማስተሰረያ ምልጃ ሲሆን የኮርማውን ደሙን ወስዶ ማስተሰሪያው ላይ ይቀባና ወደ ውስጥ ደግሞ በሳህን አድርጎ ወደ ቅድስተ ቅድስቲቱ አግብቶ ምልጃው በዚያ ንፅሁ የበግ ደም ይማለድ ነበረ:: በጭራ ደግሞ ደሙን ነክሮ ጉባኤው በመገናኛው ድንኳን በታደመው ህዝበ እስራኤል ላይ ይረጭ ነበር:: እግዚአብሄርም ያንን አይቶ ነበር የህዝቡን ኃጢያት ላያይ የዛን የበጉን ንፁህ ደም አይቶ ይቅር ይላቸውና ይማለዱ ነበር:: ፈጥና የሚያጠፋት ሳይኖር ቁጣው እንዳትነድድባቸው:: እንደዛ ግዜው ሁሉ ሊቀ ካህናችን የሱስ ክርስቶስ የካህናት አለቃ በሰማያት የበለጠ መስዋእት ይዞ ሊገባ ግድ ሆነና በገዛ በከበረ ደሙ በኪዳኑ ታቦት እንደሚረጭ እነነበረ ሁሉ በላይ በዙፋኑ ስር ይሄ የጌታችን የየሱስ የእግዚአብሄር በግ የሆነው ዘላለማዊ ህይወት ያለውን ደሙን መስዋእት ሊሆን ዘላለማዊነት የያዘውን ደም ይዞ ገብቶ ስለራሱ ሳይሆን ስለእኛ ደሙ ተረጨ! ስለነፍሳችን መዳን የተማለድነው እንግዲህ እንዲህ ባለ ሁናቴ ነው! ማዳኑ በከበረ ደሙ ሆኖ ሳለ መልአክት ያማልዱኛል የምትለው በየትኛው ደሙ ነው መልአክት የሚያማልድህ? መላእክት እኮ ደም የላቸውም! መናፍስት (መንፈስ) ናቸው! የአዳም ሃጢያት ያላወቀው የጌታ የሱስ ንፅሁ ደም ነው ብፅእት ማሪያምም እንኳን የተዋጀችበት:: መቸም ብፅእት ማሪያም ተሰቅላ ነበር አትሉም ዘንድሮ የማንሰማው የለንምና! ንፅህ ደም የጌታ የሱስ ብቻ ነው! “ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም” እብራዊያን 9:22

የራሱ የሆኑትን ሊወስድ የሚመጣውም የሱስ ክርስቶስ ነው:: በመላእክቱና ብቅዱሳኑ ታጅቦ! ቅዱሳን ማለት በጌታ ማዳን ስራ አምነው የዳኑቱ ናቸው! አንዳንዶች ይሄ ጌታ ስሙ ሲጠራ የሚያነጫንጫችሁ መንፈስ እንዲህ ያለውን መዳናችሁን እንዳትረዱና ከመረቡ ወጥታችሁ መዳን እንዳይሆንላችሁ የሚፈልገው የቀደመው እባብ ስራዬ ዳቢሎስ ነውና የጌታን ስም ጥሩና አምልጡ !

ወደ ክብራችን ጌታ ስጋችንን ለብሶ እስከ ሞት አድርሶ ፤ ከሞትም አንስቶ ደግሞ ወደ ሰማያት ያረገው ፤ እኛን ሁሉ ስጋ የለበስንን በስሙና በዚህ የማዳን ስራ መማለጃው ህያው መስዋእትነት የምናምንን ሁሉ አብ ያለነቀፋ ሆነን የሚያየን መታያችን ነው! ጌታችን የሱስ ክርስቶስ የተባረከው ተስፋችን ነው! ምስጋናውን አምጡ!…..”ካንተ በቀር በጎነት የለኝም” ዳዊት 15:2

ይህንን እንኳ የራሱን የጌታችንን የማዳኑን ጀብድ ሲተረክ ሃይማኖቱን ይዞ መጥቶ ከዚህ ከሚገርመው ስራ በላይ ሊያመናፍስ የሚጥር አለ:: እያዮ አያዮ እየሰሙም እንዳያስተውሉ እንደተባ እየሆነብን!

ንስኃ የምንገባው ይሄ ሳይገባን በህጢያታችን ሙታን በነበርን ግዜ ለወደደንና በእኛ በተዋረደ ስጋ ምሳሌ ተገኝቶ ኃጢያታችን የሚያስወግድ በግ ሆኖ ነቀፌታችንን የደህንነታችንን ተግሳፅ ለተሸከመው ነፍሱን ስለእኛ ስላኖራት እውነተኛ እረኛችንን ማዳን በቅጥ ሳንረዳና ይህንን ከገዛ ክንዱ የወጣልንን መድኃኒት ቸል ብለን ስለሞመኖራችን ብሎም በአለም ካለው እድፍን ኃጢያት ይህንን ስጋችን በደሙ እያነፃን መንፈስንና ስጋን ከሚያረክስ ነገር ሳንለይ ደሙን በማክፋፋታችን ነው:: ንስሃችንን ከክፋት መንገድ ተመልሰን በብዙ እንባ በዚህ ተስፋ ተጠብቀን የበጎች እረኛ የሆነው የህይወታችንን ጌታ በፅድቅ አለምን ኮንነን እንድንሰደድ ነው:: ተመሳስሎ መኖር አቁመን ተለይተን ስለመኖር ስንወስን ነው ንስኃችን ለፍሬ የሚበቃው! ንስኃ አለም መስለን ሳይሆን ጌታን መስለን አለምን ስለ መኮነን ነው:: የጌታንም የሙሽራችንን መምጣት በጉጉት እየናፈቅን ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ አስሬ እንደሚያሮጣት ወደ ፀሎት ስፍራችን መሮጥ ነው:: ዋላ ቶሎ ቶሎ ውሃ እንደሚጠማት ለዚሁም ጉዳይ ከወሃው ምንጭ እንደማትርቅ እኛ እዛው የኀያው ምንጭ የሆነው ጌታችን ስር ሆነን የመንፈስ ርሃብና ጥማታችንን በርሱ እንሙላ! ሲገለጥ ለሰርግ ተዘጋጅተን ኩሉን ተኩለን መብራታችንን ተግ አድርገን አብርተን አብረነው ወደ ሰርጉ ድግስ እንገባ ዘንድ እንትጋ!

ባለማመን እዚህ በሚቀሩት ላይ አውሬው ይወጣል:: የጭንቅ ግዜ በፊታችን ነው:: ሊፈታ ግዜው ቀርቧል! ጌታ የታመኑበትን ሲወስድ እዚህ የሚቀሩ ወደ ማን ዞር ይሉ ይሆን? ቃሉን ጠብቀው የኖሩ ድንገት ባይን ቅፅጰት ሄደዋልና! የፀጋውም dispensation ይነሳልና! ቃሉን ቢለመን እንኳ የሚያውቅ አይኖርም የህይወትን መንገድ የሚያመላክት ሰው አይገኝም::

በእነመክራትህና ፓስተርህ ላይ ብታላክክ ያን ቀን it will be way too late. እነእርሱም ያልስበኩት ጌታ ግን በስሙ የተጠቀሙትን ስሙን ለራሳቸው ክብርና ዝና የእግዚአብሄር ሰው በተባሉበት they might have used His holy name for now, the might even perform miracles, however, on that day, He will say to them “ጌታ ሆይ በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህ ታምራትን አላደረግንምን ሲሉ ”ሂዱ ከዚህ እኔ አላውቃችሁም” ይልና በተስፋው ቃል የታመኑትን የማይታየውን አምላክ በእምነት የታዘዙለትንና ታማኞች አገልጋዮቹን ግን ” እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ማቴዎስ 25:34 ይላቸዋል!

አሁንስ ምርጫን ምንድን ነው? ማን ነው?

“እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ?” ዳዊት 4:2

እስከመቼ ነው ልባችን የሚከብድ??

ሊዲያ ዘውዱ

#ንስሃግቡ

#ሰባሱባኤ