ልደተ ውልደት

0
382

በበረት ግርግም የተወለደልን ልደቱን እንድናከብር ወይስ እኛም ከእርሱ ዳግም ልንወለድ?

መወለዱን ስናስብ የኃጢያት ስርየት ሊሆንልን በሰው ምስል መገኘቱ፤ ስጋን ለብሶም በተዋረደው በጎሰቆለ፥ በሚታመም በሚራብ፥ በሚጠማ በሚጨነቅ፥ የሞት ጣር በሚያስፈራራው……. በባሪያ መልክ ተገኝቶ ሞትንም ድል ነስቶ ዘለአለማዊነትን ሊያላብሰን፤ የማይበሰብስ እንድንሆን እሱ ባነፃው ከሃጢያትም በዋጀው ስጋው ያው አንዱ መንፈሱ እሱን እራሱን ጌታችን የሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሳው ያው ያው ያው መንፈስ፤ ድንጋይ ሳይንከባለልለት ከፈኑን ሳይፈቱለት ሹልክ ብድግ ብሎ በግዜም ሆነ በሞት ላይያዝ ዳግም በትንሳኤው አካል እንደተነሳ ሁሉ፤ ያንኑ የማዳኑን ስራ በእኛ ሊያደርግ ዘላለም ልንኖር ወዶ ሲያድነን፤ ዳግም ከማይጠፋ ዘር ወልዶ ለማይጠፋ ለማያልፈው ርስት ሲወስነን፥ ወስኖም ሲያከብረን፥ አክብሮም ሲያፀድቀን ልደተ ቀን ብለን ልደቱን ልናከብርለት ሳይሆን እኛ ከእርሱ እንድንወለድ በእውነት ቃል አስቦ ሊወልደን እንጂ! በግዜ የማይወሰነው እሱ ለአመታቶቹም ቁጥር የሌለውን ጌታ በአህዛብ ወግ ልደት ልናከብርለት ለእድሜው ቁጥር ያለው ይመሰል ሌላ “በአል” ወግና ስርአት አይደለም የሰጠን ህይወትን እንጂ:: “አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” ዳዊት 102:27

ይልቅ እራሱ ጌታ በያንዳንዳችን በእኛው የስጋ ልብ ግርግም ውስጥ ሊወለድ ገና አለውና መመረጣችን ለዚሁ ነው! ተወልደንም በመንፈሱ ለቤዛ ቀን እንድንታተም ነው:: እኛም ልክ እንደሱ ከፈን ፍቱ ግንዛት ሳይባል፥ ቆፍሩ አውጡዋቸው ሳጥን ይከፈት ሳይባል ፤ መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ሹልክ ብለን የማይበሰብስ ሆነን በአይንም ቅፅበት ተለውጠን ልንገናኘው በአየር፤ የተዘጉና የተለሰኑ መቃብራት እንደተለሰኑና እንደተዘጉ ሹልክ ብለን ሰማያዊ ሆነን ግዜም ላይወስነን ቁጥርም ለዘመናችን ላይኖር እንለወጣለን እንሄዳለን አብረነውም እንነግሳለን:: በእርግጥ በወንጌል እንደምናነብበው ጌታ ለሶስት ቀን በመቃብር ሲውልና ሲያድር ሴቶቹ ወደ መቃብር በመጡ ግዜ “ህያውን ከሙታን መካከል ለምን ትፈልጉታላችሁ? እርሱ በዚህ የለም” ያላቸው መልአክ ድንጋዮን አንከባሎ ወደ ውስጥ ያስገባቸው ሴቶቹ ትንሳኤ ምስራች እንዲናገሩ አይተው እንዲያምኑ እንዲመሰክሩ እንጂ ለጌታ ድንጋዮም አልተንከባለለ ግንዛትንም ፈቺም አልመጣም:: ሃዋሪያው እንዳለው በብልሃት ተረት ሳይሆን ያዮትን ሊያወሩ ምስክርነቱ እንደዚያ ሆነ! “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤” 1ኛ ዮሃንስ 1:1-2

በሌላም ስፍራም እንዲሁ በመልእክቱ ሃዋሪያው እንዳለ “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” 2ኛ ጴጥሮስ 1:16 ትንሳኤና ህይወት ይረጋገጥላቸው ዘንድ በተረት ብልሃት ሳይሆን በአይን የታየ በእጅም የተዳሰሰ የተረጋገጠ ትንሳኤውን በድፍረት ሊያወሩት እንዲሆንላቸው!

እናም ልደት ማክበሩን ትተህ ለራስህ ከመንፈሱ ተወለድ ቶሎ:: የራስህን ግርግም ባዶ አድርግና አስረክብ! በአንተ ውስጥ ይወለድ ዘንድ ግርግሙን ስጥ! በአንተ መወለዱን የአለም መድኃኒትም በአንተ ውስጥ መኖሩን በሰዎች ሁሉ ፊት እየታየ የንጋቱን ኮከብ ተከትለው ወደ አንተ መጥተው በህይወት ቃሉ ሊወለዱ በደረቁ አጥንቶች ላይ ልትናገርባቸው ምስክር ትሆን ዘንዳ የሚሰሙና የሚያዮህም እነእርሳቸውም ሊለውጡ የአለም መድኃኒት በእኛ ድንግል ልቦች ላይ ሊወለድ አንቺ ቤቴልሄም የይሁዳ ከተማ ተብሎ ከማንም አታንሺም እንደተባለ እኛም ሙልአታችን ክርስቶስ ሆኖልን የተናቅን ስንሆን በምርጫ የሆነ ሃሳቡን ሲያፀና የአለምን ጥበብ ሲያዋርድ ባንዳችም እንዳንጎድል አምላክ በእኛ እንዲሆን አማኑኤል ተብሏልና! ኢየሱስም መልሶ፡— እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡ አለው። ዮሃንስ 3:3

ይወለድ በአንተ ፍቀድና:: ተወለድ በእርሱ ሁንና! ዳግም ተወለድ እርሱን እንድትመስል:: መንፈሱን ተቀበል ሞት እንዳይዝህ!

የውልደቱ ምስራች ዋናው ታላቁ ተልእኮ ይሄ ነው! ልደቱን ልናከብርለት ለአመታቶቹ ቁጥር ለዘመኑም ፍፃሜ የለውም! መንግስቱም ዘላለማዊ ነው! ለታላቅነቱ ፍፃሜ የለውም!

በዚህ ቃል ላሳርግ :-

“የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።” 2ኛ ጴጥሪስ 1:2-4

የተስፋው ክብር ተካፋይ እንድትሆኑ ጌታ በልባችሁ ግርግም ይውለድ ዘንድ በአምላኬና በአዳኜ በዘላለማዊው ንጉስ በነፍስ ሁሉ ጌታ በየሱስ ስም ስለእናተ ፀሎቴ ይህ ነው!

በልባችሁ ግርግም ባዶነት የክብር ንጉሱ ይግባ ይወለድበት!

ሊዲያ ዘ ወንጌል