Sad day in the Amhara struggle!

0
924

አንጋፋው አርበኛ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ዛሬ ታህሳስ 13 ቀን 2011 ዓ•ም አረፉ

ህዳር 23 ቀን 2011ዓ•ም ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ለቤተሰብ ጉብኝትና ለሚዲያ ስራ የመጡት በሩሲያና በአሜሪካ በሚዲያው ዘርፍ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱት አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ በድንገት ማረፋቸው ተረጋግጧል።

ትናንት ታህሳስ 12 ቀን ከረፋዱ 4 ስዓት አካባቢ”ከሰዎች ጋር ቀጠሮ አለኝ”ብለው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ አለፍ ብሎ መነን ት/ቤት አጠገብ ከሚገኘው ከእናታቸው ወ/ሮ አሳመነች ይማም ቤት በመውጣት እንደሄዱ የተገለፀ ሲሆን ከቀኑ 9 ስዓት ተኩል ሲመለሱ ጥሩ የጤነኝነት ስሜት ላይ እንዳልነበሩ ቤተሰቦች ተናግረዋል።

የቀረበላቸውን ምግብ ቀማምሰው እንደተውት እና የድካም ስሜት ይነበብባቸው እንደነበር የገለፁት ቤተሰቦቹ በመሀል ከአስር ስዓት በኃላ ሁለት እንግዶች መጥተው ሲያጫውቱት መቆየታቸውን ነግረውኛል።

ወ/ሮ እታፈራሁ ካሳ “ጋዜጠኛ ደምስን እያዋሯቸው በነበሩበት ጊዜ ከፊታቸው ላይ የእንቅልፍና የድካም ስሜት ያነበቡ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን ደምስ ከመቀመጫቸው ተነስተው”ጠዋት ስለተነሳሁ ትንሽ ልተኛ”በማለት ወደ መኝታ ክፍላቸው መግባታቸውን አይቻለሁ ብለዋል።

በመጨረሻም ምሽት 1 ስዓት አካባቢ ከመኝታቸው በመነሳት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እራት የበሉት ጋዜጠኛ ደምስ ከእራት በኋላ ግን ከውጭ ከአንዲት የስራ ባልደረባቸው ጋር ለረዥም ስዓት በስልክ እያወሩ ወደ መኝታ ክፍላቸው እንደገቡ ነግረውናል።

ጋዜጠኛ ደምስ ከአሜሪካን አገር ይዘውት ከመጡት የ8 ዓመት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ልጃቸው ገላውዲዮስ ጋር የተኙ ሲሆን ልጃቸው እንደነገረኝ ሌሊት ላይ ደም የተቀላቀለበት ትውከት ታመው ነበር።

ዛሬ ታህሳስ 13 ቀን “ያለወትሮው አረፈደ” በሚል ወደ መኝታ ክፍሉ የገባችው እህታቸው ወ/ሮ አዜብ አቶ ደምስ በለጠ አልጋው ላይ “በደረታቸው ተኝተው” ደም የተቀላቀለበት ትውከት ሲያዩ በድንጋጤ ወደ በር በመውጣት ድረሱልኝ በማለት መጮኋን ተከትሎ በርካታ የጎረቤት ሰዎች ወደ አልጋቸው በመግባት ተሸክመው ወደ ህክምና እንደወሰዷቸው ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ሳሙኤል አብርሀ የተባሉ ጎረቤት “ጩኸቱን ሰምቸ ከሰዎች ጋር በመሆን ወደ አልጋ ክፍላቸው ስንገባ ጋዜጠኛ ደምስ በጀርባቸው ተንጋለው ነበር፣ መሞታቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፣ ሰውነታቸው ግን ቀዝቅዞ ነበር” ብለዋል።

በመጨረሻም ዛሬ ከማለዳው 3 ስዓት ላይ ጋዜጠኛ ደምስን ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የወሰዷቸው ሲሆን ሀኪሞቹ ተረክበው አስታማሚዎችን ካስወጡ ከ30 ደቂቃ ቆይታ በኋላ አስታማሚዎችን በመጥራት “የሞተ ሰው ነው ያመጣቹህ፣ ከሞተ ቆይቷል “በማለት አስከሬኑን እንዳስረከቧቸው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ መነን ት/ቤት አካባቢ ተወልደው ያደጉት ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ የደም ግፊት መድሀኒት ከመውሰድ ውጭ ሙሉ ጤነኛ የነበሩ የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ አሟሟታቸውን በተመለከተ ከማዕከላዊ በመጡ የምርመራ ቡድን አባላት ዛሬ ከቀኑ 10 ስዓት አካባቢ አስከሬናቸው ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል የተወሰደ መሆኑ ታውቋል።

ከ30 ዓመታት በላይ በሩሲያና በአሜሪካ የቆዩት ደምስ በለጠ በጋዜጠኝነት ሙያ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሲሆን በአሜሪካን በ1997 ዓ•ም ንጋት የተባለ የኤፍ ኤም ራዲዮን በባለቤትነት አቋቁመው ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ከማድረሳቸው ባሻገር ላለፉት ሁለት አመታት ያህል የአማራ ድምፅ ራዲዮ (አድራ) ዋና አዘጋጅ በመሆን እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ በቅንነት፣በታማኝነትና በከፍተኛ ወገንተኝነትና ተነሳሽነት ሲያገለግሉ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

ታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ•ም ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ጋር በነበረኝ ቆይታ እንደዘገብኩት የአማራ ህዝብ እርስ በርስ ሳይከፋፈል በአንድ የአማራ ማንነት ጥላ ስር ተሰባስቦ የህልውና ትግሉን በማጠናከር መዳኛ መንገዱን እንዲፈልግ ጥብቅ ወገናዊ ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።

አባይ ዘውዱ