“የማያስተውል ህዝብ ይገለበጣል” (ሊዲያ ዘ-ጊዮን አማራ)

0
1037

መብት ትርጉሙ ላልገባው ህዝብ አምባገነንነት መልሱ ነው::

መብት ለውጥ እያለ ዛሬ ሰው በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሚያራግበው መብትም ለውጥም ባልሆነ ነገር ነው:: መታሰሩ በግፍ ሆኖ መፈታቱ እንዴት መብት ይባላል? የተፈታኸው እዛው ምንም ሳታደርግ አንከብክቦ ወዳሰረህ ስርአት ውስጥ ነው ያው ምንም የፖሊሲም ይሁን ስርነቀል ብሎም በጥገናም የተሻሻለ ነገር ወደ ሌለው መብት የለሽ ስርአት ውስጥ ነው መልሰው የከተቱህ:: አሳን መልሶ በዛው በተበከለ ባህር ውስጥ እንደመክተት ያለ ነገር ነው::

እና ምንም ያየነው ለውጥ የለም:: ሰው ያላግባብ ታሰረ ያለምንም ምክኒያት በቶርች ተጠበሰ ከዛም ያለምንም አመክኒዮ ተፈታ:: ደስ እንዳለው አንድ ስርአት የሚያደርሰው ጭቆና ነው:: እኔ በራሴ ያለምንም ምክኒያት አስረውና ገርፈው ቢያስወጡኝ የወጣሁ ቀን የሚኖረኝ ስሜትና ንዴት በእስር ወቅት ከነበረው በአንዲት ኢንች አትለወጥም:: ሂደቱ በሙሉ ኢፍታዊና ጨቋኝ ኢ-ሰብአዊ ነውና!

ግን የዘመኑ ፖለቲካዊ “ፋሽን” ከአሜሪካን የተቀዳ በቀዳዳ ሱሪ ላይ አዲስ ጨርቅ የሚለጥፍ ሆኖ አንድ ተዋናይ ሰው ብቅ ብሏል:: ከአሜርካን ያላቅም መንጠራራት የተቀዳ State dinner እና ሜዳል መሸላለም የጀመረው የአብይ/ወያኔ አስተዳደር የዶናልድን ስታይል በኦባማ ለዘብተኛ ንግግር አዳቅሎ በማንነት ቀውስ ራስሮ አገሩንም አብሮ እያቃወሰው ይገኛል::

በምገኝበት አገረ አሜሪካን ቦራክ ኦባማንም ሆነህ ዶናልድንም ሆነህ ተሻግሮ ሬገንን ሆነህ ዘልቀህም ቡሽ ብሎም ክሊንተንን ሆነህ የምትላት አንድ ነገር አለች “Washington is corrupt” “ዋሽንግተን በጣም የተመሳቀለ ጉበኛ ነው” ” I will change Washington” ብለህ ነጥለህ ትመታለህ:: ሲስተሙን ያባቶች እያልክ አሰራር ላይ ብቻ ታተኩራለህ ምንም እንኳ አሰራሩን የወለደው ስር አት system ቢሆንም ቅሉ:: ልብ መባል ያለበት ህዝብ ሲስተሙ ይቀየር የሚል ነገር ጋር እንዳይመጣ ሲስተሙ ተማክሎ የሚሰራበትን ዋናውን ስፍራ ታማዋለህ:: አሰራር ላይ ትኩረት እንዲደረግ ብዙኃንን ታነሆልላለህ:: ወዲያውም “የለውጥ ሰው” (change agent) የሚል ታፔላ ታስለጥፋለህ ነሁላላውን ብዙኃኑንም ታሰልፋለህ “ለውጥ ለውጥ ለውጥ”…. ምን ይለወጥ ስትል? ምን አይነት ለውጥ? ስንል ያው በገሌ የሆነ ነገር ነው::……” thirty years of the same failed policy must change” ይቀጥላል ሰው ያጨበጭባል … ”by the people, for the people” rhetoric after rhetoric….. በማናለብኝነት ጥቁር በጠራራ ፀሀይ እየገደልክ By the people, for the people”…. የስርአትን ግማት አፍንጫ ይለምድና ሰው ይደነዝዛል::

ዛሬ ዶናልድን ለውጥ ያመጣል ብሎም የሚለው በተመሳሳይ ያው አንድ አይነት መነሁለል ሰለባ ሆኖ ነው:: ትራምፕ በስደተኞች ላይ ያደረገው አዲስ የሚመስለው ”immigrant family separation” ዲሞክራቶች በቢል ክሊንተን ግዜ ያሳለፉትን ህግ ነው ዛሬ ዶናልድ የሚተገብረው:: ከዛም ለጥቆ በኦባማ ሁለት ተርም ያሳለፉትን ይህ ህግ ነው ትራፕ ግፋ በለው የሚልበት ዛሬ:: ምክኒያቱም አንድ አይነት ሰዎች ሁለት ጎራ ከፍለው የተቧቀሱ መስለው ለአንድ አጀንዳ ስለሚሰሩ የሚሆነው ሁሉ ሁለቱም ዲሞክራቱም ሪፓብሊካኑ የመከሩበት ነው በጀርባ:: እናም ዛሬ የኛው አቢይ “ሙሰኞች ነን” “ሽብርተኞች ነን” እያለ ምክር ቤቱን እንደ Whitehouse ሲሰድበው ይውላል:: የተሰዳደቡ የተናቆሩ መስሎ ያንኑ አጀንዳ ግን ያስቀጥላል:: …. ያው ወያኔ ያሳለፈው ህግ አማራን ማጥፋት በሚል ዛሬም አማራ ይፈናቀላል:: አማራ ዛሬም ለፈፅሞ ጥፋት ተቀጥሮ አለ::

መብት ስለሌለ ሰው ታሰረ ተገደለ፣ በባዶ እጁ ለሰልፍ የወጣ በጥይት አረረ፣ በቶርቸር ስብእናው ተናጋ እና ዛሬ የእስረኛ መፈታቱ ወደ እዛው ነባር ስርአት ውስጥ መቀላቀሉ የሚያሳየው የበለጠ ያለብን አደጋ ነው የመብት ጥሰትና ማናለብኝነት:: እንዴት ህዝብ በጅምላ ያብዳል? ነገሩ ድሮም ህዝብ በጅምላ እንዳበደ ነው:: ጌታችንን “ስቀለው ስቀለው” እያሉ ሌባ በርባንን ያስፈታ ነው ህዝብ በኛ አልተጀመረምና ተፅናኑ! እንዳበደ ነው ብዙኃን! ጤነኛ ሆኖ አያቅም!

“የማያስተውል ህዝብ ይገለበጣል”
**************************************

“ሰላማዊ ድጋፍ ሰልፍ” እያለ ዛሬ ህዝብ የሚያብደው ምንም የታየው ነገር ኖሮ ሳይሆን የጩኸት ሰለባ ሆኖ ነው:: ብዙኃኑ አእምሮው የገደል ማሚቱነት ስራ ስለጀመረ የሚሰማውን እንጂ የሚያየውን አገናዝቦ ሊረዳ አልቻለም:: ለምን? ማስተዋሉን ጆሮ በመስጠት ስላስነጠቀ ነው:: ብዙኃን መገናኛው ለሚያወራው ካላጨበጨበ ብቸኝነት ይሰማዋልና ነው:: ዋሽቶ አጀብ ቢያበዛ ስለሚመርጥ ወዳጅነቱን በውሸት መሰረት ላይ ያደርጋል:: በውሸት ላይ ውሸት መደረብ ግድ እያለ ይሄዳል አሁን መቃወም መሰረት መነቅነቅ ስለሚሆን ዝምታን መደበቂያ ያደርጋል::

በሰልፍ ሊወጣ ያኮበኮበው ወዶ ገብ ደጋፊ “ዲሞክራሲን ለማስቀጠል” “ጥገናዊ ለውጡን” በመደገፍ ነው:: ልብ ሊባል የሚገባው እዚህ ጋር ላስቀጥል የሚለው ዲሞክራሲም ሆነ መብት የሌለ መብትና ዲሞክራሲ ነው:: በኢ-ፍታዊነት አስሮ በኢ-ፍታዊነት እና አባገነንነት ያሰሩትን መፍታት ያለምንም ካሳና ይህንን አይነት ኢፍታዊነት ያደረሱ አካሎች በስልጣን እርከናቸው ላይ እንደተቀመጡና አገር በሚያሽከረክሩበት ሁኔታ ነው ያለው ህዝብ ግን ለውጥ የመጣ መስሎታል:: የለውጥ መሲህ አድርገው ያመጡት ሰው እንዲህ ያለውን ቲያትር የሚተውን ሰው ነው:: ለውጥ ሳይመጣ ልጠግን ብሎ ድጋፍ ሊሰጥ የሚወጣ ያበደ ብዙኃን ሆነን በጅምላ አብደን በጅምላ ብንሰለፍ ምን ይገርማል?! “አብይ ጋር አብሬ እቆማለሁ” የሚለው ህዝብ በተደረገለት ንግግር ልቡ እንደ ሰም የቀለጠበት ብዙኃን ዝግጁነቱ ለአምባገነን ነው:: ገና የመብት ትርጉም በኤለመንተሪ ደረጃ ያልተረዳ ህዝብ ነን:: ለውጥ ምን እንደሆን አናውቅም::

ትንሽ (remotely) ለለውጥ ዝግጁ ብንሆን ኖሮ አብይን “ግዜ እንስጥ” እንደምትሉት ግዜ ሰጥታችሁ እግር በእግር የሚደርገውን በሚዛን ላይ በማስቀመጥ በሂደቱ ውስጥ እንደ ክብደቱ ነገሮችን እየመዘኑ በጠነከረ ክሪቲክስ አቅጣጫ ማስያዝም በተቻለ ነበር:: ከአሁኑ አብይን ትናገሩና ዋ እየተባለ ማስፈራራት ተጀምሯል:: በግድ ሰልፍ ውጡም እየተባሉ ማስፈራሪያ እየተላከባቸው ያሉ ብዙዎች አሉ:: ይሄ አንባገነን ለማንገስ የሚደረግ ጉዞ እንጂ ሌላ አይደለም::

ሲጀመር ወደ ስልጣን እንኳ የመጣው በመመረጥ አይደለም:: ህዝቡ ግን የመረጠው ያህል ነው ድጋፍ የሚያሳየው:: በዚህ ሂደት ምርጫ የሰጠው አንድ አካል ብቻ ነው ያም ህውሀት ነው:: በድጋሚ:- አብይን መርጦ አምጥቶ የሾመው ህውሀት ነው!

እና ሳትመርጥ የመረጥክ የመሰለህ ነሆለሉ ህዝብ ሆይ፥ ሳትጠየቅ የተጠየቅህና ባንተ ውዴታና ፍቃድ የተሾመልህ የምታስመስል ከርታታ ብኩኑ ሆይ ከእንቅልፍህ የመንቂያ ሰአት አልፏል:: ስትነቃ ሰንሰለቱ መልሶ ቀውሮ ያስተኛሀል::

ባድሜን በዚህ እየሰጠ በዛ ሱማሌ ጋር integrate እናድርግ ሲል የሚያቧችር ህዝብ እኛ ብቻ ነን:: ሶማሌዎች በድህረ ገፆች የሚፅፉትን ላየ ከነሱም የህሊና ንቃታችን ታች መሆኑን ይሳበቃል:: እስኪ አንብቡ ሶማሌውና ግብፅ ወጣቶች የሚፅፉትን አንዳንዴ… ሶማሊ እራሷ ሶስት ቦታ ተበጣጥሳ የምትይዝ የምጨብጠው ባጣች ሰአት ኢንቲግሬት አድርገን ገለመሌ በሚል የህፃን ወሬ ይደለላል የኛ ህዝብ እነሱ ግን እንዲህ አደጋ ላይ ተጥደው እንኳ የአብይን ጉብኝት “ምን ፍለጋ ነው” የመጣብን በማለት ሲያጥላሉና ሲያራክሱ አንበናል:: የለበሳትን የዚያድባሬን ካኪ እንኳ ሳይቀር ተፀይፈው “ለምን በአገሩ ደንብ ሱፉን ለብሶ አይመጣም” ነው ያሉት:: አጉል መተሻሸቱ unappetizing ሆኖባቸው ቅፍፍ እንዳላቸው ከብዙኃን መገናኛ ላይ ባሰፈሩዋቸው መልእክቶች ለማንበብ ችያለሁ:: እንደኛ ያለ በግ ህዝብ የትም ላገኝ አልቻልኩም:: ከሱማሌ ኃላ ተሰልፈናል በንቃተ ህሊናችን willing ignorants ነንና! የግብፅም ወጣት መሳቂያ አድርጎት ነው የከረመው የአብይን ጉብኝት:: ነፃ ናቸዋ! የራሳቸው ወንድሞች ለምን ሀሳብ አንፀባረቃችሁ በሚል አይዘምቱባቸውማ:: ነፃነትን እየተለማመዱ እየኮመቱ በመሰላቸው መንገድ ፖለቲካው ያበጥራሉ:: ጥሩም የሆነ የፖለቲካ ቅኝት አላቸው:: ወደ እኛ ስንመጣ ወይ ለግምቦት -1 ቲፎዞ ነው ወይንም ለወያኔ ያደረ ነው አሊያም የአብይ (ወያኔ) አራጋቢ ነው…. ከዚህ የወጣ አስተያየት ያለው ሰው እንዳበደ ውሻ አባረን ካልነከስን ትላላችሁ::

እናም ዞምቢ ሆኖ መቀጠል ቢያሻህ አምባገነንህን ሹም በላይህ:: ትንሽም ቢሆን መንቃት ከቻልክ ደግሞ በኤሊ ፍጥነትም ቢሆን የነፃነት ጎዳናን መጀመር ተስፋ ይኖረዋል::

ባለማስተዋል እንደቂጣ ሰባ ግዜ ተገለባበጥክ:: አይበቃህም? እንቅልፍ ሲበዛ ሞት እኮ ነው?! ትንሽ ንቃና ትንሽ እስኪ ኑር ለዘላለም ከማሸለብ በፊት? ሞክረው እስኪ?