አማራ የለም ማለት ኢትዮጵያም የለችም

0
961

አንድን ነገድ ነገድ የሚያሰኘው መስፈርቶች አሉ:: ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ስነልቦና ነው፤ እነዚህ መስፈርቶች ደግሞ ለሁሉም በአለምዙሪያ ላሉ ማህበረሰቦች በመስፈሪያነት ያገለግላሉ:: አንድ ነገድ በጣም ስላደገ ብሎም በስልጣኔ ስለተራቀቀ ነገድ የሚያሰኘውን ማንነቱን የሚሻገርበትና የሚገባበት ሌላ ምንም አይነት ማንነት የለም:: ሊኖርም አይችልም:: በስልጣኔ እና እድገት መምጠቅ አንድን ነገድ ነገድ የሚያሰኘውን መስፈርቱን እንዲለቅ አያደርገውም ሊለቅም አይቻለውም:: ይሳነዋልም!

ብዙ ግዜ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የተለመደ አባባል አለ:: አንዳንዶች በዘፈቀደ አንዳንዶችም ለተንኮል የሚጠቀሙበት አባባል ነው እሱም ምንድን ነው አማራ ኢትዮጵያን በመመስረት ባደረገው የአገር ግንባታና ማዋቀር ሂደት ውስጥ ከ”ዘር” አልፎ ወደ “ኢትዮጵያዊነት” ልቋል የሚባል ምሁራዊንትም ሆነ ቀለም የጎደለው ግልብ አባባል ነው:: ከነገድ የሚልቅ ዜግነት በየትም አለም የለም:: ሊኖርም አይችልም:: ነገድ የለም ማለት ባጭሩ ያ አገር ማንነት አልባ ነው ማለት ነው:: የአገር ማንነት የሚለካው በውስጡ ባለው የነገድን ስነልቦና፣ ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ ቋንቋ ወዘተ ነውና:: ነገድን በዜግነት መለወጥ አይቻልም:: ምክኒያቱም ያ ዜግነት መገለጫ ያሻዋል:: መገለጫው ደግሞ በውስጡ ባለው የነገድ ቋንቋ፣ ወግ፣ ባህል ወዘተ ይለካል ስለዚህም ምክኒያት የአንድ አገር ሚዛን ተለክቶ በጣም የዳበረ ባህል ያለው (rich culture) ተብሎ ይሞገሳል በውስጡ ባሉት ነገዶች ባህላቸውን ዋቢ በማድረግ::

ቋንቋውን መዝነው ደግሞ በጣም ቆንጆ ቋንቋ ነው፣ የራሱ ፊደል ያለው ወዘተ ተብሎ ይነገርለታል:: ስነልቦናውንም እንዳዩት ነገዶች ፀባይ አይተው ይመዝናሉ እናም እንግዳ ተቀባይ (hospitable) ህዝብ ተብሎ ይሞገሳል ማለት ነው:: ስለሆነም ውስጡ ያሉትን ነገዶች ካልፋቅሁና ደፍጥጬ አንድ ማንነትን አለብሳለሁ ማለት የዜግነትና የነገድ ለየቅል ያለውን ሳይንስ አለመረዳት ያሳያል::

እና ይሄ ከነገድ/ዘርነት ወደ ዜግነት አደግን የሚባል አባባል ለአንድ አገር ማንነት ሰለባ ምክኒያት ይሆን እንደሆን ነው እንጂ ለዛ ለምንለው ዜግነት የበለጠ የሚያበረክተው ነገር አይኖረውም:: ያንን ዜግነት ግን ጎዶሎ ያደርገዋል:: ጎዶሎ ማድረግ ብቻ አይደለም ያንኑ ዜግነት አደጋ ላይ ይጥለዋል:: እንዴት ሲባል ያ ዜግነት ነገድ ከሌለው በነገዶች የተደገፈ ማንነት ካልሆነ ማንም እየመጣ እኔ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ ነው እያለ ጋናውም፣ ቡርኪና ፋሶውም ሁሉም መጥቶ ነኝ በማለት ብቻ ዜግነትን ሊወስደው በቻለ ነበር::

ነገር ግን አንድ ሀገር በማን ገንቢነት፣ በነማን ተዋቅራ እንደቆመች ታርክ አሳባቂ አድርጋ ትይዛለች:: ቱርክ አርመን ምድር ወሮ ቢገባ እስከ አሁን ምድሪቱ የአርመን ለመንበሯ አሳባቂው ታሪክ ብዙ ነው:: ደስ የሚለው ግን ቱርኮች እራሳቸው አገራቸውን ሲያዞር በኩራት ነው የሚናገሩት በወረራ የአርመንን መሬትና የጥንት ግሪክ መሬትን ገፎ እንደገባ:: የድል ታሪካቸው አድርገው ታሪክ ይደሰኩራሉ::

በዚህ በአሜሪካን እንኳ የአሜርካዊያንነት ስሜትን ሰፋሪዎች ማጎልበት ነበረባቸው፤ የነገዶች ማንነት ጠንካራ ማንነት እንዳይፈጠር ተሰዶ የመጣ ድብልቅ ህዝብ ስለሆነባቸው ብዙ ጦርነትን በመሳታፍ በራሳቸው ትንኮሳ ከጀመሩት ሌላ አገራትን ለማገዝ በሚል ሰበብ የገቡበት ሁሉ ምክኒያቱ ጥብቅ አገራዊ ስሜት ለመፍጠር ነው፤ ነገድ አልባ መሆኑ ትልቅ ክፍተት ሊሞሉት ስላልቻሉ:: ድብልቅ ህዝብ ደግሞ “አቦ አታካብድ” “ፍቅር ያሸንፋል” ምናምንየሚል ዘዬ እየተጠቀመ የሀገርን ጥቅም በውሉ አይረዳም ከመደባለቅና በብዙ ማንነት ወጎች መታጀቡን ብቻ ያወድሳል:: በሄደበት መኖር ይችላል:: በማንነት ስስ ነው::

ወደ እኛው ኢ-ሳይንሳዊ ወደሆነው ሀሳዊ የአንድነት ፖለቲካ ስንመጣ ሰላሳ አመት ሊሞላት ባለችዋ የሞኝ ብሂላቸው “አማራ የለም” እያሉ መደስኮር የሂትለርን አማካሪ ስልት ዋቢ በማድረግ ይመስላል:: “ውሸትን በጣም አተልቆ መናገር ሲውል ሲያድር ከውነት ይቆጠታል ይታመናል ” የሚል የጆሴፍ ጎቢልስ ምፀት “If you tell a lie big enough and keep repeating it , people will eventually come to believe it. ሲጠቀሙ መሆኑ ነው::

ነገር ግን እነኝህ “ምሁር” የተሰኙ በብዙ ምሁሮች ኪሳራ ብሎም በአገራችን ባጠቃላይ ያለውን የንቃተ ህሊና ኪሳራን በመመርኮዝ “አማራ የለም” ማለት ተመልሶ እራሳቸው ፊት ላይ የፈነዳ ችግር ሆኗል:: አንድ ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ቢኖር አማራ ከሌለ ኦሮሞ የለም ማለታቸው ነው፣ ትግሬም የለም፣ ጋሞ የለም ወዘተ ማለት ነው:: ለምን የተባለ እንደሆነ እያንዳንዱ ነገድ የሚዋቀረው ከአንዱ ብሄር አንፃር ነው:: ይሄ ትግሬ ነው ተከዜን ይዘን ስንወርድ ያለው አገረ አማራ ነው ሲባል አንፃራዊነትን በመጠቀም ነው:: ትግሬን ከአማራ ለመለየት ደግሞ እላይ የጠቀስኳቸውነገሮች እናመጣለን ቋንቋ፣ ባህሉ፣ ወጉ፣ ታሪኩ፣ ስነልቦናው እናመጣና እናይበታለን::. በለቅሶ በደስታው ያለውን ስነልቦናዊ ሂደትና አገላለፅ እናያለን:: ያን ግዜ ይህንን ህዝብ ከዛኛው ህዝብ በዚህ በዚህ በዚህ ይለያል እንልና ከአንዱ አንፃር አንዱን እናነጥራለን ማለት ነው::

እናም አማራ የለም ስትሉ ኦሮሞ የለም፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ጋሞ የለም እያላችሁ ነው ማለት ነው:: ባጭሩ ትልቁን መልእክት ስናየው ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም የሚል እንግሊዛዊ ጣሊያናዊ ባንዳ ስሪት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ በአገር በቀል በቅጥረኞቻቸው ሲካኃድ እናያለን ማለት ነው:: ይህ ደግሞ የማሞ ቂሎ ተረት ተረት እንጂ ታሪክ ሊሆን አይችልም ምርምርም ጥናትም አይደለም:: ከወሬነት አያልፍም:: እና የምድጃ ስር ታሪክ የምትወዱ ከሆነ በዳቦ ቆሎ አጅቦ ማንም ይህንን ሊሰልቅ ይችላል ነገር ግን እንደ ምርምር እንደ ጥናት አድርጋችሁ ሳይንሳዊ ላድርግ ስትሉ ፍንዳታው ፊታችሁ ላይ ይሆናል:: ማፈር ነው የሚሆነው:: መቶ ሚሊዮን ህዝብንም በተዘዋዋሪ መስደብ ይሆናል:: ይህ አባባል ፀረ-ኢትቶጵያም ነው! ፀረ- ህዝብም ነው::